Loading color scheme

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አጀማመር

የሜኖናይት ሚሽንና ቻሪቲስ እ.ኤ.አ. በ1954 የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ የሚሰጥ ቡድን ወደ ናዝሬት (አዳማ) ከተማ ላከ፡፡

እኤአ በ1946 የሜኖናይት ሚሽን በናዝሬት ከተማ የሚገኝ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ሕንጻ ለህክምና አገልግሎት እንዲውል ወደ ሆስፒታልነት በመቀየር መጠቀም ጀመሩ፡፡ በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ የድሬሰር ት/ቤት በመክፈት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትም በተጓዳኝ ይሰጥ ነበር፡፡ እኤአ ከ1950-1958 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በበደኖ፣ በደደር፣ በወንጂ፣ በአዲስ አበባና በናዝሬት ከተሞች ተከፈቱ፡፡ ከዚሁ ጋርም የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ተከፈቱ፡፡ ከተጠቀሱት አገልግሎቶች ጐን ለጐን የወንጌል ሥርጭት ሥራ እየተከናወነ ነበር፡፡ እኤአ በ1951 የመጀመሪያዎቹ ዐሥር አማኞች የውሃ ጥምቀት ወሰዱ፡፡ እንግዲህ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደተመሠረተች የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በደርግ መንግሥት በነበረው የስደት ዘመን በተለያዩ ከተሞች የነበሯት የአምልኮ ቦታዎች (ሕንጻዎች) የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በደደርና በናዝሬት ከተማ (አሁን አዳማ ይባላል) የነበሩ ሆስፒታሎች ቢወረሱም የእግዚአብሔር ሥራ ግን ሊታሰር አልቻለም፣ እንዲያውም እየሰፋ ሄዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ስደቱ ስትገባ በነበራት የአባላት ብዛት የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ በዐሥር እጥፍ ጨምሮ ተገኝቷል፡፡

የእግዚአብሔር መንፈስ ብዙዎችን ለወንጌሉ ሥራ በመቀስቀስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ የወንጌል ሥርጭትና ደቀመዛሙርትን የማፍራት ሥራን በተጠናከረ መንገድ ማካድ ቀጠለች፡፡ ለዚህ ሥራ ያመች ዘንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ በአጥቢያ፣ በክልልና በቀጣና እንዲደራጁ ይህም በዋና ቢሮ አስተባባሪነት ጽ/ቤቶች እንዲደራጁ በማድረግ በየደረጃው መሪዎችን በመሾም የእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ እንዲስፋፋ አደረጉ፡፡

ታሪካዊ ሁነቶች

በእያንዳንዱ አጥቢያ የወንጌል ሥርጭት፣ የትምህርትና ሥልጠና፣ የእረኝነት፣ የዲያቆናትና የልማትና ርኅራሄ አገልግሎት ዘርፎች አሉ፡፡ እነዚህ ዘርፎች በውስጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎት ንዑሳን ክፍሎች አሏቸው፡ በየክልሉ ደግሞ የወንጌል ሥርጭትና ቤተ ክርስቲያን ተከላ፣ የትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም የእረኝነት አገልግሎት ዘርፎች ሲኖራቸው እንደየክልሉ ሁኔታ ሌሎች የአገልግሎት ንዑሳን ክፍሎች ይኖራቸዋል፡፡ ይኸው አደረጃጀት በቀጣና ላይም በተመሳሳይ መልኩ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ዋናው ቢሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ አደረጃጀት ያለውን የአገልግሎት እንቅስቃሴ በማስተባበር የሚመራ እንደመሆኑ መጠን የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነትን በመተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም ሌሎች መመሪያዎች በትክክል ተግባራዊ መሆናቸውን በመከታተል እንደ አንድ የክርስቶስ አካል ተያይዞ ለማገልገል የሚያመቹ አካሄዶችን በማስቀመጥ ታላቁ ተልእኮን እየተወጣ ይገኛል፡፡ የዋናው ቢሮ በአጠቃላይ በፕሬዚዳንት የሚመራ ሆኖ በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ በመንፈሳዊ ዘርፍ ዋና መምሪያ በሥሩ የእረኝነት፣ የትምህርና ሥልጠና፣ የወንጌል ሥርጭትና ቤተ ክርስቲያን ተከላ፣ የሕግ ታራሚዎች የወንጌል አገልግሎት መምሪያዎችን ይመራል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የሰው ኃይልና አስተዳደር እንዲሁም የበጀትና ሂሳብ መምሪያዎች ለፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ተጠሪ በመሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት የሚመራ ቢሮ ነው፡፡ በልዩ ልዩ መመሪያዎች ሥር የልጆች፣ የወጣቶች/የከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት ተማሪዎች፣ የእህቶች፣ የሰላምና እርቅ፣ የኦሮምኛ ትምህርት፣ የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ንዑሳን የአገልግሎት ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

በአመራር አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ጠቅላላ መሪዎች ጉባኤው የበላይ ወሳኝ አካል ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሂደት በቅርበት የሚመራ የአገር ዐቀፍ/የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሪዎች ጉባኤ አለው፡፡ የእነዚህ የሁለቱም ጉባኤዎች ሰብሰቢ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቀመንበር/ሰብሳቢ አላት፡፡ በየቀጣናውና ክልሎችም ጠቅላላ መሪዎች ጉባኤና አስተዳደር መሪዎች ጉባኤዎች አሉ፡፡ በአጥቢያ ደረጃ ከአጥቢያ ምእመናን የሚመረጡና የአጥቢያዋን አገልግሎት የሚመሩ የሽማግሌዎች ጉባኤ አለ፡፡

 ወደ አጥቢያነት ያልደረሱ የወንጌል ሥርጭት ጣቢያዎች በአስተባባሪ ኮሚቴ መሪነት አገልግሎታቸው ይካሄዳል፡፡

 የ2009 ዓ.ም (ሴፕቴምበር 2017) የቤተ ክርስቲያኒቱ ስታቲስቲክስ እንደሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያኒቱ፡-

 • 1 ዋና ቢሮ
 • 1 የቀጣና ጽ/ቤት
 • 39 የክልል ጽ/ቤቶች
 • 1,011 አጥቢያዎች
 • 1,121 ሥርጭት ጣቢያዎች
 • 562,939 አባላት አሏት፡፡
 • የአገልጋዮችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በተመለከተ፡-
 • ወንጌላውያን 789  
 • አስተማሪዎች 188
 • መጋቢዎች 210
 • ድጐማ አገልጋዮች 373
 • ሚሲዮናውያን 312
 • የወንጌል አገልጋዮች               758
 • 1 ዓመት ለክርስቶስ               299
 • ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች 1,318

       በድምሩ                        4,197 በአገልግሎት መስክ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች አሏት፡፡

ዋናው ቢሮ በዋነኛነት የሚያከናወናቸው አገልግሎቶች

ቤተ ክርስቲያኒቷ አገልግሎቷን የምታካሂደው ከአባላት በሚሰበሰብ አሥራት፣ መባና ስጦታ ሲሆን አጥቢያዎች ላሉባቸው ክልሎችና ለዋናው ቢሮ በየወሩ ከገቢያቸው ጋር የተገናዘበ በመቶች የተሰላ መዋጮ በመላክ በክልል ጽ/ቤቶችና በዋናው ቢሮ የሚካሄዱት አገልግሎቶች ይደግፋሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥና በውጪ አገር የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያናችን አባላትን በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

 • የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ዋናው ቢሮ በዋነኛነት የሚያከናወናቸው አገልግሎቶች፡-
 • የወንጌል ሥርጭትና ቤተ ክርስቱያን ተከላ
 • ያመኑት በደቀመዛሙርትነት ሕይወት እንዲያድጉ ማገልገል
 • የቤተ ክርስቲያኒቱን አንነት መጠበቅ ሲሆኑ እነዚህን አገልግሎቶች ከላይ በተጠቀሱት የአገልግሎት ክፍሎች አማካይነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሶስት የአገልግሎት የትኩረት አቅጣጫዎች አሏት፡-
 1. የወንጌል ሥርጭት
 2. ደቀመዛሙርትን ማፍራት
 3. መሪዎችን ማሳደግ

እነዚህን የአገልግሎት የትኩረት አቅጣጫዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሏት መዋቅር ከሥርጭት ጣቢያ አንስቶ እስከ ዋናው ቢሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ታስቦ ነው፡፡

ተግዳሮቶች (Challenges)

 • ከቤተ ክርስቲያን እድገት ጋር ተያይዞ በአግባቡ (በሚፈለገው ደረጃ) በሁሉ ቦታ ተደጋጋሚ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች ለማድረግ የትራንስፖርት መኪና፣ የሥልጠና ማቴሪያል ዝግጅት፣ የአሠልጣኞች ሥልጠና ወጪዎች እጥረት
 • በየወቅቱ እየተነሱ ያሉ የስህተት ትምህርት ነፋሶች
 • የቁጥር 2 እና የባሕላዊ እምነቶች እንቅስቃሴዎች መጠናከር
 • አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ለአምልኮ ሕንጻ ቦታ የማግኘትና የመገንባት ዐቅም ማጣት
 • የመከሩ ሠራተኞች ማነሳቸው
 • ለሥልጠናና ለጉብኝት ለመስክ ሥራ የምንጠቀምባቸው መኪኖች ያረጁ መሆናቸው

 እንዲሟሉ የምንፈልጋቸው (Needs)

 • የሥልጠና ማቴሪያል ዝግጅትና የሥልጠና ወጪዎችን መሸፈን/መጋራት
 • የአጥቢያዎችና የትምህርት ተቋማትን የሕንጻ ግንባታ፣ የተማሪዎች ስኮላር ሺፕ ወጪዎችን መሸፈን
 • ለሥልጠናና ለጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪ መኪኖችን ግዢ መሸፈን/መደገፍ