Loading color scheme

 


አምላክ ሰው ሲፈጥረው

ከጥንት ከመጀመሪያው

ከፍጥርቱ ሁሉ ያስበለጠው

ሰውን ሰው ያረገው

በራሱ እንዲያስብ እንዲያደርግ በምርጫው

ስለሰጠው ነው ፈቃድን በግል በነጠላው::

ታዲያ እንደፍጥረቱ

ወይም እንደቀየው እንዳደገበቱ

አስተሳሰቡ ይለያል

ሁሉም በፊናው ያስባል::

አንድ ሁለት ሲሆን ሁለት ደግሞ ሶስት

እያንዳንዱ የራሱን ስላለው መረዳት

ያንዱ ሃሳብ ከሌላው

ቢለይ የማይገርም ነው::

ግን ቁርጥ እንደኔ ከማያስበው

አልወግንም ብዬ በሬን ከዘጋሁ

አንድ ብቻዬን ልቀር ነው::

አንተ አንቺ ቀርቶ በእናንተ ሲጠሩ

ሲሰበሰቡ ያኔ ለዓላማ ሲያብሩ

እኔ ማለት ቀርቶ እኛ እንዲሆን

አንዳንዴ ግድ ነው መተው የራስን፣ ፈቃድን።

ታዲያ ትክ ብሎ ባንክሮ ለቃኘው

የከርሞውን ህብረት የሚያንገዳግደው

እኔ ሳይተው እኛ ሊኮን ሲሞከር ነው::

ሁሉ በሠሃኑ ለብቻው ከበላ

የአንድነት የጋራ ትሪውን ከጠላ

አንዱ ወዳንደኛው እጁን ሳይዘረጋ

በቤቱ በቀየው ድንበር አበጅቶ ሌላ ካላስጠጋ

ሲኖር በየፊናው በሩቅ “ተከባብሮ”

ፍቅር ከተባለ ለየግል ተውሎ ለየብቻ ኖሮ

እስላም ክርስቲያኑ አረመኔው ሳይቀር

ሁሉም አለው የለ ወይ ይሄ አይነቱ ፍቅር::

ከሰኞ ቅዳሜ ለግል ተመድቦ

ህብረት አለን ቢባል ዕሁድ ተሰብስቦ

እንቅ አርጎ ቢያቅፍ ለትንፋሽ እስኪጨንቅ

የእጁም ሰላምታ ትከሻ እስኪወልቅ

"ወድሀለሁ" ማለት ከተሆነ ፍቅር

ወልድ ለምን ወረደ ከሰማይ ወደ ምድር?


እዛው በዙፋኑ እያለ በክብር

እወዳችኋለው ቢለን አይቀል ነበር?

ለምን አስፈለገው ከቶ

ሥጋ  ለብሶ መጥቶ

ተርቦ ተጠምቶ

ተሰዶ ተገፍቶ

መኖር ተንከራቶ

ኧረ ለምኑ ነው መገረፍ መታሰር

ቀላል አልነበር ወይ ያለ መስቀል ፍቅር::

ፍቅር እንጂ ዙፋን የጋራ አይሆንም

ክብርን ለመጠበቅ ህብረትን አይሹም

ለዚህ ለዚህማ ሁሉም

በየጓዳው አለቃ ይሁን ሹም::

ነገር ግን ህብረትን የምር ከፈለጉ

ፍቅርና ይቅርን ይዘው ለሚተጉ

ህብረት ለነሱ ናት የሰማያዊይቱ

ወልድ በመስቀል ላይ ያሳየን በሞቱ።

አንመለስ ብለን ከመንግስቱ ርቀን

በሃሳብ በግብር እርሱን እያሳዘን

እርቃኑን በመስቀል ያሰቀለው

እርሱ ይቅር ብሎን ይቅር በላቸው

ሲል ለአቡ ያስማለደው

ያን የጥል ግድግዳ ሲያፈርሰው

አንድ ነው ዓላማው

በእኛና በአብ መሃል ህብረት ሊፈጥር ነው።

አይገኝምና በነፃ ገብያ

ህብረትን አትሹት አትፈልጉት በዚያ

ከልብ እፈልጋለሁ ለሚል ግን

ንገሩልኝ ይህን

እንዲያውቀው ቁርጡን

ራስን ወይም የራስን ካላስከፈለ

ፍቅር ፍቅር አንዳይደለ::

ይጠየቅ ወልድ

ምን እንዲያስከፍል መውደድ

አዎ በእውነተኛ ህብረት

ፍቅር ይበረታል ከሞት።

 

በወንድም ግዛቸውወርቁ

   

 


የተናገሩት ከሚጠፋ

የወለዱት ይጥፋ

አሉ…….

የቃል ክብደቱን ያወቁ ያስተዋሉ

በሕይወት ማህደር ያገላበጡትን

በዘመን ሰሌዳ ላይ ያነበቡትን

ተናገሩ አበው…….

ከልጅ አስበለጠው

ቃል ኪዳን አክብደው

ነግሮ የሚረሳ ወይም የሚከዳ  እንዲመጣ አውቀው::

የሐጢአትን መጠን ቅጥነት ውፍረቱን

ወርድና ስፋቱ እጥረት ርዝመቱን

መች ነገረንና ስናነብ መጽሐፉን

አንዳንዶቹ ሐጢአት ተራሮች ቢያክሉም

ሌሎችም ኮስሰው ባይናችን ቢናቁም

ሃጢያት ሃጢያት ነው ትንሹም ትልቁም

ምስ ደመወዙ ሞት ነው ያውም የዘላለም::

ታድያ ከናቅናቸው ከመጤፍ ቆጥረን

ጥቃቅን ቀበሮዎች ያጠፉ እርሻንን

ከነሱ መሐከል ላንሳላችሁ አንዱን

ላልለምድ ወይ ልተወው የምታገለውን::

እመጣለው ያለ ቅልጥ ብሎ ሲቀር

አደርጋለሁ ያለ ኪዳኑን ሲሰብር

ተስፋ ሰጪ ተስፋን ሲያጠፋበት

ቃል ረክሶ  ባዶ ሲሆን ተረት

ጆሮማ ከመስማት አይሞላ ይሰማል

ተናጋሪ እንጂ ሰሚማ ምን ይበል::


በቤተ እግዚአብሐር አንድ ላይ ስንኖር

ከእህት ወንድማችን ከቅዱሳኑ ጋር

ምንም አንደኛችን ከአንዳችን ባይበልጥም

አንዱ ያለ አንደኛው ከቶ አይሆንለትም::

ታድያ ስናካፈል ስንሰጥ ያለንን

ከሐሳብ ከንዋይ ከግዜ ቆርሰን

ከዚያም ሻገር ብለን የነገን አስበን

ቃል ኪዳን ስንገባ አደርጋለሁ ብለን

መጠንቀቅ ያኔ ነው ነገር ሳይነገር

ካንደበት ሳይወጣ ሣይሻገር ከንፈር::

ከወጣ አንዴ ግን ከተነገረ ግን

ጠባቂ ከሌለው ቃል እኮ ይጠፋል::

የቃል ኪዳን አምላክ ከክብር ወንበሩ

ከሰማይ ሲያሰማ ድምጽ ከመንበሩ

ሲገባ ቃል ኪዳን..

ለአዳም ለሔዋን..

ከሴቷ የሚወለድ እባቡን ይረግጣል

ሸኮናው ቢቆስልም ራስ ይቀጠቅጣል::

ብሎ የተናገረው ያ ኪዳኑ እንዳያልፍ

ዘመን ሳይዘጋ ምድር ሳትታጠፍ

ልጁን በመስቀል ሰጠ

ቃል ከነፍስ በለጠ::

እንኳን የወለደ ያልወለደም ሲያውቀው

ኪዳኑ እንዳይፈርስ አምላክ እግዚአብሔርን ልጁን ካስከፈለው

ቃል ኪዳን ከመግባት ቃል ኪዳን መጠበቅ እንደምን ከባድ ነው?

 

              "አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?

              በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?

              …..በአንደበቱ የማይሸነግል፥

               …..ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም። "    

                            (መዝ ዳዊት 15)    

             

         በወንድም ግዛቸው ወርቁ