Loading color scheme

MKC Prison Ministry

 MKC Head Office has a department for Youth Ministry

 

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን

ዋናው ቢሮ

የሕግ ታራሚዎች አገልግሎት መምሪያ

አጠቃላይ ሥራ አጭር መግለጫ

  • የመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሕግ ታራሚዎች አገልግሎት እግዚአብሔር በከፈተው የወንጌል በር በሃገሪቱ ባሉት ማረሚያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 21 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዚህም አገልግሎት አያሌ ታራሚዎች ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አምነው ተቀብለዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ በማረሚያ ቤት እና ከማረሚያ ቤት ውጪ እውነተኛ የክርስቶስ አምባሳደር በመሆን የወንጌልን እውነት በመኖር እና ለሌሎችም በመስበክ የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ በተግባር በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡
  • ቀደም ሲል በነበሩት መንግሥታት የምሥራቹን ቃል በማረሚያ ቤት ውስጥ መስበክ ቀርቶ በሌላ ስፍራ እንኳን ሲናገሩ የተደመጡትና ይልቁንም የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች  በመሆናቸው  ብቻ  በማረሚያ ቤት ይጣሉ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ታሪክ ተለውጦ ቤተክርስቲያን የምሥራቹን ቃል ሰዎች በሚገኙበት በየትኛውም ስፍራ የማድረስ ነፃነት አግኝታ እነሆ በማረሚያ ቤት ውስጥ ሳይቀር ወንጌልን በመስበክ እና ደቀመዛሙርት በማፍራት አገልግሎት ተጠምዳለች፡፡ ስለዚህ ድንቅ አሰራሩ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባረከ እና የተመሰገነ ይሁን፡፡ በቤተክርስቲያን ይህን አገልግሎት  ስንጀምር በደቡቡ የሃገራችን ክፍል ባለ  በእያንዳንዱ ማረሚያ  ቤት  5-10 አማኞች ብቻ ነበሩ፡፡
  • ዛሬ በደቡቡ የሃገራችን ክፍል በእያንዳንዱ ማረሚያ ቤት ከ350-800 የወንጌል አማኝ ታራሚዎች በአንድነት ያመልካሉ፣ የራሳቸው የሆነ ትልልቅ ጸሎት ቤቶች አሏቸው፣ የበሰሉ መሪዎች እና አገልጋዮችም አሏቸው፡፡ ስለሆነም እኛ በዓመት 2ጊዜ ወደየማረሚያ ቤቱ በመሄድ ጉብኝት በማድረግ እና በማገልገል የአልባሳት፣ የመጽሐፍቅዱስ፣ የመጽሔት እና ሌሎች ቁሳቁሶች ስርጭት እናደርጋለን፡፡ በፖስታ ቤት በደብዳቤም አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጠቅላላ አገልግሎት ከምንሰጥባቸው 50 ማረሚያ ቤቶች መካከል በ21 ማረሚያ ቤቶች ውስጥ 21 የወንድ የሙሉ ጊዜና 6 ሴት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ተመድበው በየቀኑ ወደ ማረሚያ ቤት በመግባት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
  • በዋናው ቢሮ አንድ አስተባባሪ፣ ትምህርትና ስልጠናን፣ የሴት ታራሚዎችና ልጆቻቸውን አገልግሎት፣ የሰላምና እርቅ አገልግሎትን የሚያስተባብሩ፣ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሳቢ እና የጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ፣ በጠቅላላው 12 አገልጋዮች አሉ፡፡ ከማረሚያ የወጡ አማኝ ታራሚዎችን ተከትለው ቤተክርስቲያን በሌለበት በ 5 ቦታዎች ቤተክርስቲያን በመትከል እያገለገሉ ያሉ አገልጋዮችም አሉ፡፡ ስለሆነም የማረሚያ ቤቱን የወንጌል ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደራጀ መልኩ እንድንሠራ እግዚአብሔር ረድቶናል፡፡

እንዲሁም እግዚአብሔር አገልግሎቱን ተጠቅሞ በሠራቸው ታላላቅ ሥራዎች የተገኘ ፍሬና ውጤት አለ፡፡ ይኸውም አገልጋይ በመደብንባቸው በ21 ማረሚያ ቤቶች ብቻ እንኳን በዓመት በአማካይ፡- እስከ  32000 ታራሚዎችና ፖሊሶች ወንጌልን እንዲሰሙ ይደረጋል፡፡

- 1500 ታራሚዎችና ፖሊሶች ጌታን ይቀበላሉ፡፡

- 500 አማኝ ታራሚዎችና ፖሊሶች የውሃ ጥምቀት ይወስዳሉ፡፡

- በትምህርት ደረጃቸውና በህይወት ምስክርነታቸው ሻል ያለ ደረጃ ያላቸው 400 አማኝ ታራሚዎች በስነ-መለኮት ትምህርት በዲፕሎማና በሰርተፍኬት መርሐግብር የርቀት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይመረቃሉ፡፡

እንዲሁም  በማረሚያ ቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አግኝተው ደቀመዛሙርት ሆነው የተፈቱ ታራሚዎች ወንጌላዊ፣ መጋቢ፣ የቤተክርስቲያን መሪ፣ ሽማግሌ፣ ኳየር፣ ሚሲዮናዊ ሆነው በየቤተእምነቱ የሚያገለግሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

  • ከማረሚያ ቤት ወጥተውም በ 5 ቦታዎች ላይ ቤተክርሰቲያን የተከሉም አሉ፡፡ለጠቅላላ ታራሚዎች በሚሰጠው ትምህርትና የምክር አገልግሎት ተለውጠው በማረሚያ ቤቱ የምስክር ወረቀት የሚያገኙ በአመክሮ የሚፈቱና መንግስት በየዓመቱ በይቅርታ የሚፈታቸው ታራሚዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በቀለም ትምህርት ራሳቸውን የሚለውጡ በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው የሞያ ባለቤቶች የሆኑ የራሳቸው ሥራ ፈጥረው ወይም ተቀጥረው እየሰሩ ገቢ የሚያገኙና ራሳቸውን ችለው ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሥራው እጅግ ሰፊና ብዙ ፍሬ የሚታይበት ነው፡፡ ቢሆንም ግን ዛሬም በሁላችንም ፊት ተደቅኖ ያለ ጥያቄ ግን አለ፡፡
  • ‹‹በዚህ እግዚአብሔር በከፈተው የአገልግሎት በር እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ቤተክርስቲያን የሚገባንን ያህል ምን ያህል እየሮጥን ነው?›› በማረሚያ ቤት ፍቅርን አጥተው ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ያሉ፣ በፀፀትና በሐዘን ውስጥ የሚገኙ፣ ከህብረተሰቡ ተገለው በተወሰነ ክልል ለሚኖሩት፣ ከሠሩት ወንጀል የተነሳ በህሊና ፀፀት ውስጥ ለሚዳክሩት፣ ትተውት /ጥለውት/ ስለመጡት ቤተሰብና ንብረት እየተጨነቁ እረፍት ላጡት፣ ከአሁን በኋላ ምን እሆናለሁ በሚል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉት ታራሚዎች ምን ያህል መጽናናት አግኝተዋል፣ ከዚህም በላይ በኃጢአትና በልዩ ልዩ እስራት ውስጥ ያሉ የህግ ታራሚዎች ምን ያህል የወንጌል ብርሃን እየበራላቸው ጌታ ኢየሱስ ከኃጢአት እስራት እየፈታቸው ነው፣ የክርስቶስን ፍቅርና የመታደግ ሥራ በማወጅ የእርሱ ደቀመዝሙር ይሆኑ ዘንድ ምን ያህል በትጋት እየሠራን ነው?
  • በመጽሐፍቅዱስ ውስጥ ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ በስጋ ይመላለስ በነበረበት ወቅት የተናገረውን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ‹‹ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፡፡ ማንም ሊሰራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና›› ዮሐ 9፡-4 አዎን ዛሬ ቀን ነው፡፡ ብርሃን አለ፣ የምንሻውን ለማድረግ ጨለማ /ሌሊት/ የለም፡፡ ነገር ግን ጨለማው መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምድር ላይ ቆይታው በተወሰነ ጊዜ የተገደበ ስለሆነ የመጨረሻው ደወል ከመደወሉ በፊት በትጋት፣ በጥራትና በፍጥነት ከአባቱ ዘንድ የተቀበለውን ኃላፊነት ተወጥቷል፡፡ እኛም ጌታ በሰጠን ፀጋ በተከፈተው በር በአግባቡ ልናገለግልበት ይገባል፡፡